ኢትዮጵያ ከስዊዘርላንድ ጋር ትስስሯን በማጠናከር በተለያዩ ዘርፎች የመስራት ፍላጎት እንዳላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከስዊዘርላንድ ኮንፌዴሬሽን ረዳት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ስታልደር ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት አምባሳደር ምስጋኑ፤ በሀገራቱ መካከል ጠንካራ ግንኙነት መፈጠሩን ገልጸው፤ በተለይ ስዊዘርላንድ ኢትዮጵያ ምርቶቿን ከምትልክባቸው ሀገራ መካከል እንደምትጠቀስ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከስዊዘርላንድ ጋር ትስስሯን በማጠናከር በማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ አግሮ-ፕሮሰሲንግ እና የቴክኖሎጂ ዘርፎች መስራት እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ እያደገ ያለ ኢኮኖሚ እና ህዝብ ያላት በመሆኗ ትኩረት የሚሻ የወደብ ባለቤትነት ጥያቄ እንዳላት አስረድተው፤ የወደብ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ እውን ለማድረግ እየሰራች ነው ብለዋል።
በተጨማሪ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ሀገራዊ ምክክር እና የፍትህ ሽግግር ገለጻ አድርገው፤ ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላም መሆን አበክራ እንደምትሰራም ጠቁመዋል።
ፊሊፕ ስታልደር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተቋቁማ እያስመዘገበች ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚደነቅ ገልጸዋል።
እንዲሁም በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈንና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ለምታበረክተው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
ሁለቱ ወገኖች የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት በማጎልብት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተስማምተዋል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ