
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በሩሲያ ኢኮኖሚ ሚኒስትር ማክሲም ራሽቲኒኮቭ ከተመራ ከፍተኛ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።
ኮሚሽነር ዘለቀ በዚህ ወቅት፥ የግሉን ዘርፍ ለማሳደግና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር እየተተገበሩ ያሉ ሪፎርሞችንና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የሚከናወኑ ሥራዎችን አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል።
ኮሚሽነሩ መንግስት የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ሁለንተናዊ ግንኙነት በኢኮኖሚና በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ዘርፍ እንዲያድግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ማክሲም ራሽቲኒኮቭ በበኩላቸው÷ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ እና በግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ያላትን ትብብር ለማሳደግ እንደምትፈልግ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሩሲያ በማዕድን ሃብት ልማት፣ በአፈር ማዳበሪያ፣ በታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
ሀገራቱ በጋራ ሊያለሟቸው የሚችሏቸውን የኢንቨስትመንት ዘርፎችና ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመለየት የሚያስችል የኢንቨስትመንት እና ቢዝነስ ፎረም በቀጣይነት በጋራ እንደሚያካሂዱ መገለጹንም የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ኤም.ሲ