የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና (ኤ ኤፍ ሲ ኤፍ ቲ ኤ) ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረጉ በአህጉሪቱ ሁሉን ያሳተፈ ዕድገት እንዲኖር እንደሚያደርግ የአፍሪካ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተናግረዋል።
በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደው 59ኛው የአፍሪካ ልማት ባንክ የገዢዎች ቦርድ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ፥ አህጉራዊ የንግድ ልውውጥ ሲጨምር አፍሪካ በምዕራባውያን ገበያ ላይ ያላት ጥገኛነት እንደሚቀንስ ተጠቁሟል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ቡድን ዋና ጸሃፊ ቪንሰንት ንመሂሌ በዚህ ወቅት ፥ በአህጉሪቱ በሚመረቱ ሸቀጦች ላይ የገቢ ቀረጥ በማስቀረት በመላው አፍሪካ ያለውን የንግድ ልውውጥ ነፃ ማድረግ የአፍሪካን የንግድ ልውውጥ ያሳድጋል ፤ አነስተኛ የንግድ ተቋማትንም ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
በአፍሪካ ሀገራት ያለው ተጨማሪ የንግድ ልውውጥ በአህጉሪቱ ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚረዳም ነው የገለጹት።
የምስራቅ አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ ጆን ቦስኮ ካሊሳ ፥ ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት በአነስተኛ ንግድ እና በሴቶች የተያዙ ኢንተርፕራይዞች በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስር በንግድ ልውውጥ ሂደት ዙሪያ እያስተማረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
አፍሪካ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች በብዛት ያላለቀላቸው ማዕድናትና የግብርና ምርቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል ሲል የዘገበው ዥንዋ ነው፡፡
በዚህም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና በእነዚህ ምርቶች ላይ እሴት እንደሚጨምር ገልጸው ፥ ይህም አህጉሪቱ ወደ ሁሉን አቀፍ እድገት እንድታመራ እንደሚያግዝም ነው የገለጹት፡፡
ካሊሳ ፥በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ውስጥ ያለው የንግድ ልውውጥ 18 በመቶ መሆኑን ያነሱ ሲሆን ፥ በአንጻሩ በእስያ 50 በመቶ እና በአውሮፓ ደግሞ 70 በመቶ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
የብሪክስ ኒው ልማት ባንክ የአፍሪካ ቀጣናዊ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሞናሌ ራትሶማ በበኩላቸው ፥ ድርጅቱ በአፍሪካ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት በቀላሉ አህጉራዊ ንግድን ለማሳለጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኤፍ ቢ ሲ