ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፉት አሥር ወራት ከ2 ሺህ 700 ጊጋ ዋት ሠዓት በላይ ኃይል ማመንጨቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በሁለት ተርባይኖች ኃይል እያመነጨ የሚገኘው ግድቡ÷ ባለፉት አሥር ወራት ከዕቅዱ የ26 በመቶ ብልጫ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨቱ ተገልጿል።
በዚህም 2 ሺህ 152 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት ሠዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ 2 ሺህ 711 ጊጋ ዋት ሠዓት ማመንጨት መቻሉ ነው የተመላከተው።
ለአፈጻጸሙ ስኬትም ግድቡ የተሻለ ውኃ መያዙና ሁለቱ ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው ኃይል እንዲያመነጩ መደረጉ ተጠቅሷል።
ባለፋት አሥር ወራት በአጠቃላይ ከመነጨው የ16 ሺህ 900 ጊጋ ዋት ሠዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 16 በመቶ ድርሻ እንዳለው ተጠቅሷል።
የግድቡ ሁለቱ ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን÷ የሚተከሉት ቀሪ 11 ዩኒቶች ኃይል ማምረት ሲጀምሩ እንደሀገር ያለውን የማመንጨት አቅም 83 በመቶ ያሳድገዋል ተብሏል።
የግድቡ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም የሚኖረው ሲሆን÷ ዓመታዊ የኃይል ምርቱም 15 ሺህ 760 ጊጋ ዋት ሠዓት ይሆናል።
ምንጭ፦ ኤፍ ቢ ሲ