ቢትኮይን በታሪኩ ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ

ቢትኮይን የተባለው ክሪፕቶከረንሲ በታሪኩ ከ109 ሺህ ዶላር በላይ በመድረስ ከፍተኛ ዋጋ ማስመዝገቡ ተገለጸ።

እንደ ቢትኮይን ያሉ ያልተማከሉ የዲጂታል ገንዘብ አማራጭን የሚደግፉት ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዛሬ በዓለ ሲመታቸውን ከማድረጋቸው ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ኮይኖታግ ዘግቧል።

ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ታህሳስ ወር አንድ ቢትኮይን ዋጋው 103 ሺህ ዶላር ደርሶ አንደነበር የሚታወስ ነው።

የቢትኮይን ደጋፊ መሆናቸውን በይፋ የተናገሩት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በቢትኮይን ድጋፍ ተቀብለዋል ተብሏል።

በፈረንጆቹ 2008 ላይ ሳቶሺ ናካሞቶ በተባለ እና እስካሁን ማንነቱ ባልታወቀ ሰው የተመሰረተው ቢትኮይን እንደ ኤልሳልቫዶር ያሉ ሀገራት በ2021 ላይ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ መገበያያ እንዲሆን ፈቃድ አግኝቷል።

47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ” አሜሪካንን የቢትኮይን ግብይት ማዕከል እድትሆን አደርጋለሁ” ማለታቸው ይታወሳል።

ክሪፕቶ ከረንሲ በጥቃቅን ክስተቶች ጭምር ከፍተኛ የሆነ የዋጋ መለዋወጥ የሚያሳይ ኢ-ተገማች የሆነ ያልተማከለ ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓት ነው።

የዘርፉ ባለሙያዎች የአንድ ቢትኮይን ዋጋ በ2025 ከ250 ሺህ ዶላር በላይ ከፍ ሊል እንደሚችልና ለዚህም ተቋማት ለግብዓት ለመገልገል ፍላጎት መጨመር እና የተቆጣጣሪ አካላት የተሻሻለ መመሪያ ማውጣት እንደ ምክንያትነት ተጠቅሰዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው አርብ እንዲሁም ባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ ደግሞ ትናንት የክሪፕቶከረንሲ አካል የሆነውን ሚምኮይን በራሳቸው ስም ለሽያጭ ክፍት ማድረጋቸውን ዘገባው ያመለክታል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *