በ2017 በጀት ዓመት በሌማት ትሩፋት የንብ ማነብ መርሐ ግብር 375 ሺህ ቶን የማር ምርት ለማግኘት መታቀዱን ግብርና ሚኒስቴር አስተወቃ።
በግብርና ሚኒስቴር በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ የንብ እና ሀር ሃብት ልማት ዴስክ ኃላፊ አዚዛ አያሌው፤ ኢትዮጵያ በማር ምርት ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም ደግሞ 10ኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠች ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ የንብ ቀሰም እጽዋቶች፣ ከ2 ሚሊየን በላይ ንብ አናቢ አርሶና አርብቶ አደር፣ የብዝኃ የአየር ንብረት ስርዓተ-ምኅዳር፣ ከ12 ሚሊየን በላይ ህብረ ንብ ያለባት ሀገር በመሆኗ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ከዓለም 10ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በአጠቃላይ በዓመት 500 ሺህ ቶን የማር እና 50 ሺህ ቶን የሰም የማምረት አቅም እንዳለ በጥናት መረጋገጡንም ተናግረዋል።
በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ከ207 ሺህ ቶን በላይ ማር እና ከ13 ሺህ ቶን በላይ ሰም ለማምረት ዕቅድ በመንደፍ የንብ ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራው ስራ ከዕቅድ በላይ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል።
የንብ ማነብ ስራ ለሌሎች የግብርና ስራዎች ተስማሚና ተመጋጋቢ ሆኖ መልማት የሚችል ወሳኝ የኢኮኖሚ አቅም እንደሆነም አንስተዋል።
የንብ ልማት የቡና፣ የሰብል፣የቅባት እህል፣ የአቮካዶና ማንጎን የአትክልትና ፍራፍሬ የግብርና ምርታማነትን የማሳደግ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል።
በማር ምርታማነት እየተመዘገበ የሚገኘው ስኬት የወጣቶችን የንብ ማነብ ባህል በማሳደግ በስራ ዕድል ፈጠራ አይተኬ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የአረንጓዴ አሻራ እና የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርም ንቦች ከተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ደኖች፣ ከሰብሎች፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ አበባ በመቅሰም ከፍተኛ የማር ምርት እንዲያስገኙ አስችለዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ማር ወደ አውሮፓ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያገኘች ነው ያሉት ኃላፊው፥ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚፈልግም አመላክተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት 375 ሺህ ቶን ማር ለማምረት ዕቅድ ተይዟል ያሉት አቶ አዚዛ፤ የማር ምርት የወጪ ንግድን ማሳደግ የሚያስችሉ አሰራሮች እየተዘጋጁ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚመረቱ 11 አይነት ልዩ የማር አይነቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ማር የሚመገቡ ሰዎችን የስርዓተ ምግብ በማሻሻል ጤናማ እንዲሆኑ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ከሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ጋር በማስተሳሰርና የአናቢዎችን አቅም በማሳደግ የማር ቆረጣ ድግግሞሽን በአማካይ በዓመት ወደ አራት ከፍ እንዲል ማድረግ እንደተቻለ አንስተዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ