በግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያና ዩናይትድ ኪንግደምን የንግድ ትብብር የሚያጠናክር ስምምነት ተፈረመ

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከዩናይትድ ኪንግደም አሴት ግሪን ኩባንያ ጋር የተቀናጀ የወተት ልማትና የንግድ እርሻ ፕሮጀክትን ለመጀመር የሚያስችል የ600 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ።

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጄላ ሬይነር ተገኝተዋል።

በስምምነቱ መሠረት አሴት ግሪን 51 በመቶ ድርሻ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ደግሞ 49 በመቶ ድርሻ መያዛቸው ተነግሯል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፤ በዚህ ወቅት ፕሮጀክቱ ግብርናውን ለማዘመንና የቴክኖሎጂ እውቀትን ለአርሶ አደሮች ለማስተላለፍ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ለስኬታማነቱም የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ(ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ስምምነቱን በውጤታማነት ለመተግበር እንሰራለን ነው ያሉት ።

የአሴት ግሪን ቺፍ ኢንቨስትመንት ኦፊሰር፣ አልበርት ፍሪሸንላገር፤ ስምምነቱ በአፍሪካ ግዙፍ የወተት ልማት ፕሮጀክትን መተግበር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ጥራት ያለው የወተት ምርታማነትን በማሳደግና የግብርና ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማዘመን የሚጨበጥ ውጤት ለማምጣት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

የስምምነቱ ዓላማ ምርታማነትን፣ ውጤታማነትንና ዘላቂነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተሻለ የግብርና ስርዓት መገንባት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ግዙፍ ስትራቴጂክ ስምምነት በሁለት ምዕራፎች እንደሚተገበር ተገልጿል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የወተት ልማት ማቀነባበሪያ ከመኖ ልማት ጋር ያካተተ ሲሆን ለዚህም 10 ሺህ የወተት ላሞችን የሚይዝ ማዕከልን ለመገንባት ታቅዷል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የጋራ ኢንቨስትመንቱን በማስፋት የማቀነባበሪያ መሰረተ ልማቶች ወደ ተሟሉለት የጥጥ፣ የቅባት እህሎች እና የሩዝ እርሻ ለማሳደግም ግብ ተይዟል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *