በጋምቤላ ክልል የወርቅ ማዕድን ሀብት ልማትን በማዘመን ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማጎልበት የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለፁ።
በሚኒስትሯ የተመራው የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ቡድን በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ እየተከናወነ ያለውን የወርቅ ማዕድን ሀብት ልማት ተመልክቷል።
በወቅቱ ሚኒስትሯ እንዳሉት መንግስት ከወሰዳቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሞች መካከል የወርቅ ማዕድን ሀብት ልማቱ አንዱና ዋነኛው ነው።
በዚህም እንደ ሀገር ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ስኬቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በጋምቤላ ክልልም የወርቅ ማዕድን ሀብትን አዘምኖ በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማጎልበት የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን በምልከታቸው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
በተለይም በቅርቡ ተመርቆ ወደ ስራ የገባው የኢትኖ ማይኒንግ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ ሀብቱን በአግባቡ ማልማት የሚያስችል መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠርና የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ከማድረግ አንፃርም አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
በክልሉ ያለውን የማዕድን ሀብት በህጋዊ መንገድ በማልማት ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ የሚያስገኘውን ጥቅም ለማሻሻል የተጀመሩ ጥረቶች ይበልጥ ሊጠናከሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን(ዶ/ር) በበኩላቸው ክልሉ በወርቅ ማዕድን ሃብት የበለፀገ ቢሆንም ሀብቱን በሚፈለገው ልክ አልምቶ ከመጠቀም አንፃር ውስንነቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ መንግስት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የማዕድን ሃብት ልማት እየተስፋፋ መምጣቱን ገልፀዋል።
አሰራሩ እየዘመነ መምጣቱ ደግሞ ሀብቱ በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች እንዳይበዘበዝ በማድረግ ለሀገር የኢኮኖሚ ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እንዲጠናከር ያስችላል ብለዋል።
በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ በመደረጉ የወርቅ ማዕድን ሀብቱ በአግባቡ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ እድል መፍጠሩንም አብራርተዋል።
በሚኒስትሯ የተመራው ቡድን በዛሬው ዕለት ከጎበኟቸው መካከል በቅርቡ ተመርቆ ወደስራ የገባው የኢትኖ ማይኒንግ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ፣ የወርቅ ግብይት ማዕከላትና ሌሎችም ይገኙበታል።
ምንጭ፦ ኢዜአ