በኦሮሚያ ክልል እስከ አሁን 1 ነጥብ 16 ሚሊየን ቶን የቡና ምርት ተሰበሰበ

ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወነ ሥራ 1 ነጥብ 16 ሚሊየን ቶን የቡና ምርት መሰብሰቡን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በተያዘው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 6 እንዲሁም በመጀመሪያው አጋማሽ 1 ሚሊየን ቶን የቡና ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የቢሮው ምክትል እና የቡና እና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድሳኒ አሚን ገልጸዋል።

ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተከናወነው የተቀናጀ ርብርብም ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ጀምሮ እስከ አሁን 1 ነጥብ 16 ሚሊየን ቶን የቡና ምርት መሰብሰቡን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።

አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 10 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸው÷ ለዚህም ከሚጠበቀው ጊዜ ቀደም ብሎ የተስተካከለ የዝናብ ሁኔታ መኖሩን በምክንያትነት አንስተዋል።

በክልሉ የቡና ልማትና ምርታማነትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ያነሱት አቶ መሐመድሳኒ በክልሉ በ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሔክታር ላይ የሚገኝ ቡና ምርት እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በ2017 ዓ.ም 2 ነጥብ 5 ቢሊየን የቡና ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *