በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ሁለንተናዊ ድጋፍ ይደረጋል- ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ኢንቨስትመንት አማራጮች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።

የክልሉን የኢንቨስትመንት አማራጮች ከማስተዋወቅ ባለፈ ኢንቨስተሮቹ ምርትና አገልግሎታቸውን ለዕይታ የሚያቀርቡበት ለሁለት ቀናት የሚቆይ ዐውደ ርዕይና ፌስቲቫል ዛሬ በጋምቤላ ተጀምሯል።

የሁነቱ አካል የሆነ የፓናል ውይይት ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለሃብቶች በተሳተፉበት እየተካሄደ ነው።

ርዕሰ መስተዳድሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ያሉትን ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ወደ ልማት ለማስገባት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

ከለውጡ በፊት በክልሉ ሲስተዋሉ የነበሩት ያልተገቡ አሰራሮች በኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደነበራቸው አስታውሰዋል።

የክልሉ መንግስት ችግሮችን በማስተካከል የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲነቃቃ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በዚህም በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች በክልሉ ለሚሰማሩ አልሚ ባለሀብቶች የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ይቀጥላል ብለዋል።

ዐውደ ርዕይና ፌስቲቫሉ አዳዲስ ባለሀብቶችን ለመሳብና ነባር ባለሀብቶችን እንደሚያነቃቃ ጠቁመዋል።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሎው ኡቡፕ(ዶ/ር) በበኩላቸው የክልሉን ሰፊ የኢንቨስትመንት አቅም በማልማት ከዘርፉ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።

ዐውደ ርዕዩ የክልሉን ጸጋዎች በማስተዋወቅ ክልሉን ዋነኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *