በኢትዮጵያ የውጭ ባንኮች እንዲሳተፉ የሚፈቅደው አዋጅ ፀደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውጭ ባንኮች እንዲሳተፉ የሚፈቅደውን የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅ አፀደቀ።

ምክር ቤቱ በ11ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።

በዚሁ ጊዜ የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግና ለምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ቀጣይነት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የባንክ ስራ መሰማራታቸው የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ከማምጣት ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ለማሳደግ ያግዛልም ነው የተባለው።

የምክር ቤቱ አባላት የአገር ውስጥ ባንኮችን አቅም ሳያሳድጉ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት ማድረግ ይዞት ሊመጣ የሚችል አሉታዊ ተፅዕኖ የለም ወይ የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

በሌላ በኩል የምክር ቤቱ አባላት ከብሄራዊ ባንክ የቁጥጥር አቅም፣ ከአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የብድር አቅርቦት ጋር ሊያጋጥሙ ይችላሉ ያሏቸውን ስጋቶች አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በሰጡት ምላሽ፣ ረቂቅ አዋጁ የባንክ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ክፍት የሚሆንበትን ስርዓት የሚያስቀምጥ ነው ብለዋል።

የፋይናንስ ዘርፉን ክፍት ማድረግ የአገር ውስጥ ባንኮችን አቅም የሚያጠናክር እንጂ የሚያጠፋ አለመሆኑንም አብራርተዋል።

አሰራሩ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ተቀጥላ ኩባንያ እንዲከፍቱና ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር በሽርክና እንዲሰሩ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።

ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ክፍት መደረጉ የአገር ውስጥ ባንኮችን የበለጠ በማጠናከር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የድርሻውን እንዲወጣ ያስችለዋል ብለዋል።

ምክር ቤቱ የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅን በሶስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *