የሩሲያው የቢትኮይን ማይኒንግ አቅራቢ ድርጅት “ቢትክሉስተር” በኢትዮጵያ 120 ሜጋ ዋት የቢትኮይን የመረጃ ማዕከል ለማቋቋም ማቀዱን ይፋ አድርጓል (https://bitcluster.ru/mass-media/from-the-arctic-to-africa.html)።
ቢትኮይን ማይኒንግ ምንድነው?
የቢትኮይን ማይኒንግ በቢትኮይን የሚፈፀሙ ግብይቶች አስተማማኝ እና እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚረዳ ስርዓት ነው።
የመረጃ ማዕከሉ የሚገነባው በአዲስ አበባ ከፍተኛ-ቮልቴጅ ማከፋፈያ ጣቢያ ባለበት ቂሊንጦ አካባቢ ሲሆን 30,000 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ነው ተብሏል።
አዲሱ የመረጃ ማዕከል ሥራ ከወር በኋላ እንደሚካሄድ ሲገልፅ በአሁኑ ወቅት ትራንስፎርመሮች የማገናኘት ስራ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።
የመረጃ ማዕከሉ የምህንድስና እና የቴክኒክ አሰራር ዘመናዊ የሆኑ የቢትኮይን ማይኒንግ መስፈርቶችን የሚያሟሉ መሆናቸውን ሲጠቀስ ለማዕከሉ 100% የኤሌክትሪክ ኃይል ከታዳሽ የኃይል ምንጮች በተለይም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚቀርብ መሆኑ ተጠቅሷል።
የቢትኮይን ማይኒንግ ማዕከልን በኢትዮጵያ ለማቋቋም መወሰኑ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ ጥቅም አለው የተባለ ሲሆን የቢትኮይን ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ኢትዮጵያ ከዚህ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተጠቃሚ ትሆናለች ነው የተባለው።
የቢትክሉስተር ተባባሪ መስራች ሰርጌይ አሬስቶቭ “ትልቅ የሀይድሮ ፓወር አቅም ያላት ኢትዮጵያ ፥ የአለም አቀፍ ቢትኮይን ማይኒንግ አዲስ የመስህብ ቦታ እንደምትሆን ጥርጥር የለውም” ብለዋል።