የሩሲያው ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ላዳ እና ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ተሽከርካሪዎችን በኢትዮጵያ ለማምረት እና ለመገጣጠም የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ እና የላዳ የወጪ ንግድ ዳይሬክተር፣ የሽያጭ እና ማርኬቲንግ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢሊያ ሳቪኖቭ ናቸው።
አምባሳደር ሱሌማን በፊርማ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የሩሲያ ባለሐብቶች በተለይም በማዕድን፣ በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
ዛሬ በተፈረመው ስምምነት መሰረትም÷ ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የላዳን ያልተጠናቀቁ ምርቶች በመገጣጠም ሥራ የሚጀምር ይሆናል ብለዋል፡፡
በቀጣይም ግብዓቶችን በማስመጣት ተሽከርካሪዎችን ለገበያ እንደሚያቀርብም ነው ያስታወቁት።
ኢሊያ ሳቪኖቭ በበኩላቸው÷ በርካታ የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል።
የሩሲያ ኢትዮጵያ የቢዝነስ ፎረምም ከነገ በስቲያ እንደሚካሄድ ጠቁመው÷ ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ አመላከትዋል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ