ባንኮች በዚህ አመት ከውጭ ለሚላክ ዶላር የሚሰጡት ማበረታቻ ጉርሻ ሊጠናቀቅ ሁለት ሳምንት ይቀረዋል።
በመደበኛ የባንኮች እለታዊ የምንዛሬ ተመን 1 ዶላር እስከ 112 ብር ተገዝቶ እስከ 126 ብር እየተሸጠ ይገኛል
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች በየእለቱ አዳዲስ የምንዛሬ ተመን እያወጡ ነው።
የ2017 አዲስ ዓመት አስመልክቶም ባንኮች በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያውን በህጋዊው መንገድ ገንዘብ እንዲልኩ የሚያበረርታታ ተመን እያወጡ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል የሚላክን ገንዘብ ከባንኩ ለሚቀበሉ ደንበኞቹ ተጨማሪ የ6.82 በመቶ የበዓል ስጦታ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
ባንኩ ዛሬ መስከረም 15 2017 ዓ.ም መደበኛ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ የትናንት ተመኑን አስቀጥሏል። በዚህም አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ112.3957 ብር እየገዛ በ123.6353 ብር እየሸጠ ይገኛል።
ዳሸን ባንክ በዓልን ምክንያት በማድረግ ልዩ የምንዛሬ ዋጋ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም በሃዋላ የሚላክ 1 ዶላርን ከመደበኛው የምንዛሬ ዋጋ ላይ እስከ 16 በመቶ ጉርሻ እንደሚሰጥ ማሳወቁ ይታወቃል።
ባንኩ በመደበኛ የምንዛሬ ዋጋው ደግሞ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ112.3989 ብር እየገዛ በ126.4488 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን ይፋ ያደረገው።
ኦሮሚያ ባንክም በዓልን ምክንያት በማድረግ ከውጪ በሃዋላ የተላከ አንድ የአሜሪካ ዶላርን ከእለታዊ ተመን በተጨማሪ 17 በመቶ ጉርሻ እንደሚሰጥ እና በዚህም 1 ዶላርን በ126+ ብር እንደሚመነዝር ማስታወቁ ይታወሳል።
ባንኩ የዛሬ የመስከረም 15 2017 መደበኛ የምንዛሬ ተመኑን ይፋ ሲያደርግ 1 የአሜሪካ ዶላር በ112.39882120 ብር እየገዛ በ127.0106 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው የጠቆመው።
እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ የሚላክን አንድ የአሜሪካ ዶላር በ125 ብር እንደሚመነዝር ያስታወቀው ንብ ባንክም መደበኛውን (እለታዊ የምንዛሬ ተመን) ይፋ አድርጓል።
በዚህም ባንኩ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ109.7209 ብር እየገዛ በ122.8874 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጿል።
ምንጭ፦ አል አይን