በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት 10 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የእንስሳት ተዋፅኦዎች 74 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሳህሉ ሙሉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ምርትና ተዋፅኦዎች በማቀነባበር የገበያ ሁኔታን የሚደግፍ ነው።
በተጨማሪ የእንስሳት ምርትና ተዋጽኦዎ በኢንዱስትሪ ተቀነባብረው ለገበያ እንዲቀርቡ የምርምር፣ የቴክኒክና የማማከር ድጋፍ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስራዎች ሲከውን መቆየቱንም ተናግረዋል።
ባለፉት 10 ወራት 25 ሺህ 900 ቶን መጠን የእንስሳትና እንስሳት ተዋፅዎ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 24 ሺህ 200 ቶን ምርት ለማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
በገቢ ደረጃ 113 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 74 ሚሊየን ዶላር ገቢ በማግኘት የእቅዱን 65 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልፀዋል።
የእንስሳት ስጋ ምርትና ተረፈምርት 62 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር፣ ከማር 108 ሺህ የአሜሪካን ዶላርና ከሰም ደግሞ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንዲሁም ከመኖ 10 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።
ባለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት 74 ነጥብ 3 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን አስረድተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በበጀት ዓመቱ ከእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ 140 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአገር ውስጥ የምርት ግብዓት ዋጋ መናርና በመዳረሻ አገራት የተቀነባበረ ምርቶች መሸጫ ዋጋ በነበረበት መቆየት፣ የመዳረሻ ገበያ የፀጥታ ችግር፣ ህገ-ወጥ ንግድ፣ የምርት ጥራት ጉዳይ ለዘርፉ ችግር መሆኑንም ነው ያብራሩት።
የምርት መዳረሻዎችን ለማስፋት እንዲሁም ለምርቶች የተሻለ ዋጋ የሚከፍሉ አማራጭ ገበያ ለመፈለግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል የቁጥጥር ስራ መጠናከሩንና የምርት ደህንነትና ጥራትን ለማስጠበቅ ለአርሶ አደሩ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ