
የግሪክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎችን ተጠቅመው በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀርቧል።
የኢትዮ-ግሪክ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፎረም በግሪክ አቴንስ ተካሂዷል።
ፎረሙን ያዘጋጁት በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በግሪክ የኢትዮጵያ ቆንስላ እና የግሪክ አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት በጋራ በመተባበር ነው።

በፎረሙ ላይ የኢትዮጵየ እና የግሪክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ የኢትዮጵያና የግሪክ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ ወይዘሮ ወርቃፈራው አክሊሉ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገቸው ሀገር በቀል ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጭ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ እና በግሪክ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ አማራጮች እንዳሉም ገልጸዋል።

በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አቶ አሰፋ አቢዩ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የንግድና የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳላት እና ከቅርብ አመታት ወዲህ በአፍሪካ ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገበች መሆኗን ተናግረዋል።
የግሪክ ኩባንያዎችን በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩና የሀገሪቱን ምርት እንዲገዙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳጋቶ ኩምቤ በፎረሙ ኢትዮጵያ ያላትን ልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የተዘረጉ የህግ ማዕቀፎችን፣ አሰራሮችንና ማበረታቻዎችን አስመልልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ እና ግሪክ ኩባንያዎች መካከል የአንድ ለአንድ የንግድ ውይይቶች በማድረግ የሀገራቱን ትብብር ለማጠናከር ስምምነት ላይ መደረሱን በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግሪክ፣ ቆጵሮስ እና ማልታን ይሸፍናል።
ኢትዮጵያ እና ግሪክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1917 መጀመራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ምንጭ፦ ኢዜአ