‹‹የቻይናና የኢትዮጵያ ግንኙነት በሁኔታዎች የማይበገር ጠንካራ ደረጃ ደርሷል››አቶ አህመድ ሺዴ የገንዘብ ሚኒስትር

 የቻይናና የኢትዮጵያ የሁለቲዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሁኔታዎች የማይበገር ፣ጠንካራና ዘላቂ የትብብር ደረጃ መድረሱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቻይና ጉብኝት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ በሁኔታዎች የማይበገር ግንኙነት ሆኗል።

በቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መካከል ሰፊ ውይይት መካሄዱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ በውይይታቸውም የሀገራቱ ግንኙነት በሁኔታዎች የማይበገር ደረጃ ስለመድረሱ እውቅና ተሰጥቶታል ብለዋል።

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፡-ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰችበት የሁለትዮሽ ግንኙነት በዓለም አቀፍ ጥቂት ከሚባሉ ሀገራት ጋር የሚደረግ ነው፤ ከአፍሪካም ኢትዮጵያ ተመራጭ ሆናለች።

በውይይቱ የሁለቱ ሀገራት የጋራ ጥቅምን ያማከለ ወዳጅነት፣ ጠንካራና ዘለቄታ ባለው መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከስምምነት ተደርሷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከዚህ በፊት እንደነበረው የኢኮኖሚ ትብብር ብቻ ሳይሆን የደህንነትና ሌሎች ዘርፎች ላይ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በቀጣይ የሚካሄድ መሆኑ የተገለጸበት እንደሆነ ጠቁመዋል።

አቶ አህመድ፣ የአዲስ አበባ የወንዝ ዳር ፕሮጀክትና ለሌሎች በቻይና መንግሥት ድጋፍ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች ላይ ደረጃ በደረጃ ድጋፍ እንዲደረግ የሚመለከታቸው የቻይና ፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ የቻይናው ፕሬዚዳንት ውሳኔ አስተላልፈዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ለሰላምና ለኢኮኖሚው ውህደት ለምታደርገው እንቅስቃሴ ለመደገፍ የቻይና መንግሥት ቃል ገብቷል ያሉ ሲሆን፤ ውይይቱ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ውጤት ያስገኘ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ከፍተኛ የሰላምና የጸጥታ ሚና ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ፕሬዚዳንቱ ቃል መግባታቸውንም ነው አቶ አህመድ ያስታወቁት።

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፡- የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እየሠሩ ያሉትን ሥራዎች እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ መርሀ- ግብር ላይ ያለውን ስኬት በማድነቅ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።

ምንጭ፦ ኢ.ፕ.ድ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *