የባንክ ሥራ አዋጅ ምን አንኳር ጉዳዮችን ይዟል?

በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው አዲሱ የባንክ ሥራ አዋጁ በአስራ አንድ ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን 94 አንቀጾችን ይዟል።

  • በአዋጁ የመጀመሪያ ክፍል አጭር ርዕስ እና ትርጓሜን የተመለከቱ ጉዳዮች ተካተዋል።
  • በክፍል ሁለት ስለ ባንክ ሥራ ፈቃድ የሚያብራራ ሲሆን

የባንክ ሥራ ፈቃድ ለማግኘት መሟላት ስላለበት መስፈርት፣ ፈቃድ ለማግኘት ስለሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች፣ ፈቃድ ስለመስጠት፣ የባንክ ሥራ ስለመጀመር፣ የፈቃድ እድሳት፣ ፈቃድ የተሰጣቸውን ባንኮች ዝርዝር ስለማሳተም እንዲሁም ቅርንጫፍ ወይም ንዑስ ቅርንጫፍ ስለመክፈት የተመለከቱ ድንጋጌዎችን አካቷል።

  • በክፍል ሶስት የውጭ ዜጎች በባንክ ሥራ ስለሚሳተፉበት ሁኔታ ተቀምጧል

ይህ ክፍል ጠቅላላ ድንጋጌዎችን፣ የውጭ ባንክ ተቀጥላ በባንክ ሥራ ስለሚሳተፍበት ሁኔታ፣ የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ በባንክ ሥራ ስለሚሳተፍበት ሁኔታ እና እንደራሴ ቢሮ ስለሚሠራው ሥራ የተመለከቱ ጉዳዮችን አካቷል።

በዚህ ክፍል ማንኛዉም የውጭ ባንክ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በባለቤትነት የሚይዘው የውጭ ባንክ ተቀጥላ እንዲያቋቁም ወይም የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ እንዲከፍት ወይም እንደራሴ ቢሮ እንዲከፍት ወይም የባንክ አክሲዮኖችን እንዲይዝ ሊፈቀድለት እንደሚችል ይደነግጋል።

የውጭ ባንክ ያልሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች ወይም በውጭ ሀገር ዜጋ ባለቤትነት የተያዙ የኢትዮጵያ ድርጅቶች የባንክ አክሲዮን እንዲይዙ ሊፈቀድ እንደሚችል ያስቀምጣል።

ማንኛውም ስትራቴጂክ ኢንቨስተር በአንድ ነባር ወይም አዲስ የሀገር ውስጥ ባንክ የሚይዘው ቀጥተኛ የአክሲዮን ድርሻ ከባንኩ አጠቃላይ የተፈረመ ካፒታል ከአርባ በመቶ መብለጥ እንደማይችልም በዚሁ ድንጋጌ ተቀምጧል።

የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በጉልህ ሊጠቅሙ የሚችሉ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶችን ለማምጣት እንዲሁም በቀዉስ ላይ ላለ ባንክ ዕልባት ለመስጠት እና የፋይናንስ መረጋጋትን ለማስጠበቅ ብሔራዊ ባንክ ጥሩ የፋይናንስ መሠረት እና ስም ያለዉ የዉጭ ሀገር ባንክ አንድ ሥራ ላይ ያለን የሀገር ዉስጥ ባንክ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ መጠቅለል እንዲችል በልዩ ሁኔታ ሊፈቅድ እንደሚችልም ተካቷል።

  • ክፍል አራት ስለ አክሲዮኖችና የባለአክሲዮኖች ጉባኤ ያስቀምጣል

ይህ ክፍል ስለ አክሲዮኖች አይነት እና የአክሲዮን መዝገብ ስለሚያዝበት ሁኔታ፣ አክሲዮን የመያዝ ገደብ፣ በባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ የብሔራዊ ባንክ ድርሻ ምን እንደሆነ፤ ድምፅ የመስጠት እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ መብቶች ስለሚገደቡበት ሁኔታ የተመለከቱ ድንጋጌዎችን በውስጡ አካቷል።

  • ክፍል አምስት ስለ ባንክ ሠራተኞችና ዳይሬክተሮች ይገልጻል

የባንክ ዳይሬክተሮች በተሻለ እውቀት እና ውጤታማ በሆነ መንገድ ሀላፊነታቸዉን እንዲወጡ እና የባንኩን አላማ እንዲያስፈጽሙ ለማስቻል ነጻ እና ገለልተኛ የሆኑ ግለሰቦችን (Independent Directors) በቦርድ ውስጥ ማካተት እንዳለባቸዉ የሚያስገድድ ድንጋጌ በአዲስነት ተካቷል፡፡

  • ክፍል ስድስት የፋይናንስ ግዴታዎችና ገደቦች

ባንኮች ካላቸዉ ጥሬ ገንዘብ እና በብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ ካደረጉት ውጭ ያሉ ሌሎች ንብረቶች ብሔራዊ ባንክ በየጊዜዉ በሚወስነዉ መሰረት እንደሚካተቱ በሚገልጽ መልኩ የተሻሻለ ሲሆን ባንኮች በአለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አደራረግ ደረጃ መሰረት ተጨማሪ የመጠባበቂያ ገንዘብ ሊይዙ እንደሚችሉ የሚፈቅድ አዲስ ድንጋጌ እንዲገባ ተደርጓል።

  • ክፍል ሰባት ስለ ፋይናንስ መዝገቦችና የውጭ ኦዲተር ሹመት ይዘረዝራል

ብሔራዊ ባንክ የአንድን ባንክ የውጭ ኦዲተር ሹመት በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ካለመገኘት፤እንዲሁም የታወቁ ሙያዊ አሠራሮችን ካለመከተል ጋር በተያያዘ መሰረዝ የሚያስችለዉ ሥልጣን እንዲኖረዉ ዓለም አቀፍ ልምድ እና ተሞክሮን መሠረት በማድረግ በረቂቅ አዋጁ እንዲካተት ተደርጓል።

  • ክፍል ስምንት መረጃ ስለ መስጠት፣ ሪፖርት ስለ ማቅረብ እና በባንኮች ላይ ስለሚካሄድ ምርመራ ያትታል

በዚህ ክፍል ሪፖርት ስለ ማቅረብ እና መረጃ ስለ መስጠት፣ በባንኮች ላይ ስለሚካሄድ ምርመራ፣ የምርመራ ሪፖርት ስለሚዘጋጅበት እና አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃዎች ስለሚወሰድበት አግባብ የተመለከቱ ድንጋጌዎች ተካተዋል፡፡ በተለይ ምርመራን መሠረት በማድረግ ባንኮች ላይ በብሔራዊ ባንክ ሊወሰዱ የሚችሉ የማስተካከያ እርምጃዎችን በተመለከተ በተዘጋጀዉ ረቂቅ አዋጅ ሰፋ ባለ መልኩ በማየት በነባር አዋጁ ከተጠቀሱ እርምጃዎች በተጨማሪ ሌሎች ዘርዘር ያሉ አዳዲስ የእርምጃ አይነቶችን አካቷል፡፡

  • ክፍል ዘጠኝ ውህደት፣ ግዥ፤ እና ወሳኝ የባለቤትነት ድርሻ እንዲሁም ሀብት እና ዕዳ ስለ ማስተላለፍ የተብራራበት ነው

በዚህ ክፍል በተደነገጉ የተለያዩ አንቀጾች ከብሔራዊ ባንክ በቅድሚያ የጽሑፍ ፈቃድ ካልተሰጠ በስተቀር ማንኛውም ባንክ በፈቃደኝነት ውህደት መፈጸም እንደማይችል፣ ብሔራዊ ባንክ ችግር ያለባቸው ባንኮችን ለማዳን እና/ወይም ይበልጥ ጠንካራ የሆኑ ባንኮች እንዲፈጠሩ ለማስቻል በአስገዳጅነት የሚደረግ ውህደት እንዲፈጸም ማድረግ እንደሚችል፣ በአንድ ባንክ ወሳኝ የባለቤትነት ድርሻን የሚፈጥር ማንኛውም የአክሲዮን ዝውውር ወይም ግዥ በአክሲዮን መዝገብ ላይ ከመመዝገቡ በፊት በብሔራዊ ባንክ መጽደቅ እንዳለበት እንዲሁም በመደበኛ የሥራ ሂደት ካልሆነ በስተቀር ከብሔራዊ ባንክ አስቀድሞ የጽሑፍ ፈቃድ ሳይሰጥ ማንኛዉም ባንክ ሀብቱን ወይም ዕዳውን ለሌላ ባንክ ሊያስተላልፍ እንደማይችል በአዋጁ ተካቷል።

  • ክፍል አስር ስለ እልባት፣ ፈቃድ ስለ መሠረዝና ስለ መፍረስ የሚደነግግ ሲሆን

በዋናነት ለፈቃድ ስረዛ ስለሚያበቁ ጉዳዮች፣ የመፍረስ ውሳኔ የተላለፈባቸዉ ባንኮች በተመለከተ የንብረት አጣሪ በመሾም የንብረት ማጣራቱ ተግባር ስለሚከናወንበት ሁኔታ፣ ባንክ ሲፈርስ በቅድሚያ ስለሚፈጸሙ ሥርዓቶች፣ በይገባኛል ጥያቄዎች ላይ ሰለሚሰጥ ውሳኔ፣ ስለተፈቀዱ የይገባኛል ጥያቄዎች የመጨረሻ ኘሮግራምና ድልድል እና የአከፋፈል ቅደም ተከተል፣ በፈቃደኝነት ስለሚከናወን የባንክ ማፍረስ ዉሳኔ አተገባበር፣ እና ስለንብረት የማጣራት ተግባር መጠናቀቅ የተመለከቱ ድንጋጌዎች ተካተዋል።

  • ክፍል አስራ አንድ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው

የመጨረሻው ክፍል የሆነው ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ሲሆን፣ ከላይ ባሉት ክፍሎች ውስጥ ሊካተቱ የማይችሉ የተለያዩ ጉዳዮችን በአንድ አቅፎ እንዲይዝ ተደርጓል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *