በ2016 በጀት ዓመት ከቡና ወጪ ንግድ 1 ነጥብ 43 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳህለማሪያም ገ/መድህን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ከቡና ምርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም መሰረት የቡና ምርት ጥራትን ማሳደግ፣ የግብይት ሰንሰለቱን ማዘመንና የውጪ ምንዛሬ ማስገኘት ላይ በትኩረት መሰራቱን አንስተዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ299 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ 1 ነጥብ 43 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ ቡናን ወደ ውጪ መላክ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በታሪክ የመጀመሪያው ከፍተኛ ገቢ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ቡና ወደ ውጪ ከተላከባቸው ሀገራት መካከል ሳዑዲ ዓረቢያ፣ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ቤልጂዬምና ደቡብ ኮሪያ ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዙ አመልክተዋል፡፡