
ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ያለውን ድርድር ለማጠናቀቅ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጓን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) ጨምሮ የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት ተደራዳሪ ኮሚቴ አባላት ከዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ ጋር ተወያይተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ውይይቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን የሚደረገውን የድርድር ሂደት ለማጠናቀቅ ዕቅድ ይዛ እየሰራች መሆኑን በተመለከተ ከዋና ዳይሬክተሯ ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን ከ23 ዓመት በፊት ድርድር መጀመሩን አስታውሰው፥ እስካሁን አራት የሥራ ላይ ቡድን ውይይቶች ማካሄዷን ተናግረዋል።
የፊታችን መጋቢት በጄኔቫ ለሚደረገው አምስተኛው የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባም በቂ ዝግጅት ማድረጓን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ሀገራት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ መሰጠቱን ጠቁመው፥ 18 አንቀጾች ተዘጋጅተው መቅረባቸውንም ገልጸዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከዓለም ንግድ ድርጅት ጋር ድርድር ለማጠናቀቅ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉ ማረጋገጣቸውን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ