ኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅ ኢንቨስትመንት ለሚሳተፉ ባለሃብቶች ምቹ መዳረሻ መሆኗን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን ገለጹ።
የግሎባል ላይነን የጨርቃጨርቅ ፎረም በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን፤ በፎረሙ አስራ አምስት ሀገራት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በርካታ አምራች የሰው ኃይል ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል።
ይህም ለኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው ያብራሩት።
ከዚህ በተጨማሪም ጥጥን ጨምሮ ለጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን የሚያበቅል አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት አላት ብለዋል።
መንግስት የወጪ ንግድን ለመደገፍ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ማቋቋሙንም ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ጅቡቲ ባቡር መስመር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም አቀፍ ገበያውን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥሩ ጠቁመዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ