ኢትዮጵያና ጀርመን በልማት፣ በቴክኒክ እና ምጣኔ ሀብት ዙሪያ ያላቸውን ትብብር የሚያጠናክር ምክክር አካሄዱ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በጀርመን ውጭ ጉዳይ ቢሮ የፖለቲካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል እና የሊቢያ ልዩ መልዕክተኛ ከሆኑት ክርስትያን በክ (ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙርያ መክረዋል።
በዚህ ወቅት አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ኢትዮጵያና ጀርመን በልማትና በቴክኒክ ትብብር እንዲሁም በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት አውስተዋል።
በዘርፎቹ ያለውን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን ማሳደግ የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ አምባሳደር ምስጋኑ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የፕሪቶርያው ስምምነት አፈጻጻም ሂደት፣ ብሔራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ላይም ገለጻ አድርገዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች የጋራ ተጠቃሜነት ባላቸው በአህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙርያ መምከራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ