የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦትስዋና የቱሪስት መዳረሻ ወደ ሆነችው ማኡን ከተማ በረራ ጀመረ።
በማስጀመሪያው መርሃ-ግብር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስጻሚ መስፍን ጣሰው ፣የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻ በኢትዮጵያ የቦትስዋና አምባሳደር ተብሌሎ አልፈርድ ቦአንግ ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት አየር መንገዱ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ መዳረሻውን በየጊዜው እያሰፋ ይገኛል።
አየር መንገዱ አፍሪካንና አፍሪካዊያንን ለማስተሳሰር የያዘውን ውጥን ከግብ ለማድረስ በትጋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በአየር ትራንስፖርት አፍሪካን በማስተሳሰር ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና መፋጠን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ነው ያሉት።
አየር መንገዱ በረራ የጀመረባት ማኡን ከተማ በአፍሪካ 65ተኛ መዳረሻው መሆኗን አስታውቀዋል።
አየር መንገዱ ወደ ቦትስዋና ዋና ከተማ ጋቦሮኒ በረራ የሚያደርግ መሆኑን በማስታወቅ የማኡን ከተማ በቦትስዋና ሁለተኛዋ መዳረሻ መሆኗን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓም ወደ ሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታውን በረራ መጀመሩ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉት 147 የሚጠጉ አውሮፕላኖች 136 ዓለም አቀፍና 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።
ምንጭ፦ ኢዜአ