በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትልልቅ ኩባንያዎች በማዕድን ምርት እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ናስር ሙሐመድ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ የተፈጠረው ሰላም እና በአገር አቀፍ ደረጃ የተወሰደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትልልቅና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጭምር በማዕድን ምርት እንድሰማሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
በአዲስ አበባ በተካሄደው 3ኛው የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ላይ በክልሉ የሚገኙ የማዕድን ሀብቶችን በማስተዋወቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በክልሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማግባባት ስራ መከናወኑን ገልፀዋል።
በርካታ ኩባንያዎችም በማዕድን ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳሳዩ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጠቅሰዋል።
በክልሉ የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ ሜድሮክ ኩባንያ በመተከል ዞን በማዕድን ምርት ለመሰማራት በዝግጅት ላይ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
ሌሎች አነስተኛ ማዕድን አምራቾችም በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ወደ ስራ መግባታቸውንም ጠቁመዋል።
በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለማዕድን ዘርፉ ትልቅ መነቃቃት ፈጥሯል ያሉት አቶ ናስር፤ መንግስት ለወርቅ አቅራቢዎች ማበረታቻ ማድረጉ በዘርፉ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
ክልሉ በአምስት ወራት ውስጥ 1 ሺህ 100 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማስገባቱንም አቶ ናስር እንደማሳያ ጠቁመዋል።
ክልሉ የማዕድን ሀብቱን እንዲጠቀም እና በሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ያለውን ድርሻ አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ዘርፉ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ የሚገኘው ኩርሙክ ወርቅ አምራች ኩባንያ በኤክስፖው ላይ የራሱን ዕቅድ ያቀረበ እና ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ የሀገሪቷን የኢኮኖሚ አቅም ይደግፋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ