በኬንያ ቀዳማዊት እመቤት ራቼል ሩቶ የሚመራው ‘ማማ ዱይንግ ጉድ’ የተባለው ድርጅት ሴቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማብቃት ከሁዋዌይ ጋር ጥምረት ፈጥሮ እየሰራ ነው።
ድርጅቱ ከ14 ሺህ በላይ የሚሆኑ የኬንያ ሴቶች ማኅበራትን በዲጂታል ክህሎት ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ከሁዋዌይ ኬንያ ጋር የመግባቢያ ሠነድ ተፈራርሟል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የ ”ማማ ዱይንግ ጉድ” ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ጆን ቹሞ ከሁዋዌይ ጋር የፈጠሩት ጥምረት ኬንያ እስከ ፈረንጆቹ 2030 ለማሳካት ከያዘችው ራዕይ ጋር የተጣጣመ ነው ብለዋል።
ጥምረታቸው ሴቶችንም ተደራሽ በማድረግ ሁሉም ሰው ደስተኛ፣ የተሟላ እና የተለወጠ ሕይወት የሚኖርበትን ፍትሃዊ ማሕበረሰብ የመፍጠር ዓላማ ያነገበ መሆኑን ገልጸዋል።
የሁዋዌይ ኬንያ ምክትል ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ስቲቨን ዣንግ በበኩላቸው፥ የኬንያ ሴቶችን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማገዝ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ተዘግቧል።
ምንጭ፦ አፍሪካ ቴክ