የጣልያን ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ከጣልያን የኮንፊንደስትሪያል ቤርጋሞ ፕሬዚዳንት እና ዋና ዳይሬክተር ጋር ተወያይተዋል።
በዚህ ወቅትም የጣልያን ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል።
የጣልያን አምራች ድርጅቶች የተለያዩ ማሽነሪዎችን በማምረት፣ በምግብ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በኬሚካል፣ በፕላስቲክ እና በፓኬጂንግ እንዲሁም በብረታብረት ዘርፍ ላቅ ያለ ልምድ እንዳላቸው ተጠቁሟል።
ድርጅቶቹ በዓመት እስከ 20 ቢሊየን ዩሮ ምርት ወደ ውጭ ሀገራት የመላክ አቅም ያላቸው ሲሆን÷ በቀጣይ ሌሎች የአውሮፓ ባለሃብቶችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የማስፋት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
አቶ መላኩ በኢትዮጵያ ሰፊ የገበያ እድል፣ ከፍተኛ አምራች ኃይል፣ በቂ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የተሟላ የሎጂስቲክ አቅርቦት እንዲሁም የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮች መኖራቸውን አስረድተዋል።
ለአምራች ኢንዱስትሪ የሚደረጉ ማበረታቻዎች እና ሌሎች የኢንቨስትመንት መደላድሎች እንዳሉ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተለያዩ አምራች ኢንዱትሪዎች የተሰማሩ የጣልያን ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቁመው፥ በቀጣይ ባለሃብቶች በምግብ ኢንዱስትሪው ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸው እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፡ ኤፍ.ቢ.ሲ