ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ለማጠናከር ትሰራለች – የአገሪቱ የውጭ ንግድና ልማት ሚኒስትር     

ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና በኢንቨስትመንት መስክ ያላትን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራ የአገሪቱ የውጭ ንግድና ልማት ሚኒስትር ቪሌ ታቪዮ ገለጹ።

የውጭ ንግድና ልማት ሚኒስትር ቪሌ ታቪዮ በዚህ ሣምንት በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ይህንንም ተከትሎ ሚኒስትሩ ቪሌ ታቪዮ ኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለበርካታ ዓመታት ያስቆጠረ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁ የፊላንድ የልማት ትብብር አጋር አገር መሆኗን ጠቅሰው በውኃ፣ በግብርና እንዲሁም በትምህርት ዘርፎች በትብብር እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።

ፊንላንድ በኢትዮጵያ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካው መስክ የሚካሄዱ የሪፎርም ሥራዎችን ለማገዝ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2021 እስከ 2024 የሚቆይ የ75 ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ቀርጻ እየተገበረች ነው።

ፊንላንድ በውኃ ዘርፍ በምታደርገው ድጋፍ በኢትዮጵያ የንጹህ ውኃ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት መቻሉን ገልጸው በተመሳሳይ በግብርናና በትምህርት የትብብር መስኮችም አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ነው የገለጹት።

በዚህ የድጋፍ ማዕቀፍ በኢትዮጵያ የተሰሩት ሥራዎች የእስካሁኑ አፈጻጸማቸው ስኬታማ መሆኑንና ትብብሩን በቀጣይም ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተለይም ከኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በቅድመ ጥንቃቄ የትንበያ መረጃ ሥራዎች ላይ በጋራ ለመሥራት እቅድ መኖሩን ጠቁመዋል።

በዘመናዊ ግብርና ፊንላንድ የተሻለ አፈጻጸም ያላት አገር መሆኗን ጠቅሰው በዚህ ዘርፍ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

በሌላ በኩል ፈንላንድ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋን ለማጠናከር እንደምትሻ ገልጸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ትሰራለች ነው ያሉት።

ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የፊንላንድ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ኅብረት የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን አገራቸው ፍላጎት እንዳላት ጠቅሰው ለዚህም ይሰራል ነው ያሉት።

በተለይም የኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ መስክ የበለጠ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲያገኝ ለማድረግ በትምህርት ዘርፍ ፊንላንድ ድጋፏን እንደምታጠናክር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለማቋቋም የምታከናውነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ሊበረታታ የሚገባው የአረንጓዴ ልማት ሥራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የጀመረችው አገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን ፊንላንድ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

ሚኒስትሩ ቪሌ ታቪዮ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ በትምህርት ዘርፍ የመምህራን አቅም ግንባታ የሚውል የ5 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ሥምምነት አድርገዋል።

ኢትዮጵያና ፊንላንድ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ1959 መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *