
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 1 ነጥብ 54 ትሪሊየን ብር መድረሱ ተገለጸ።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ አጋማሽ ሥራ አፈጻጸም ገምግመዋል።
በበጀት ዓመቱ እስከ የካቲት 16 ቀን 2017 ድረስ የተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ከ350 ቢሊየን ብር በላይ መድረሱን አቶ አቤ በግምገማው ላይ ገልጸዋል።
አጠቃላይ የባንኩ ተቀማጭ የገንዘብ መጠንም ከ1 ነጥብ 54 ትሪሊየን ብር በላይ መድረሱን አንስተዋል።
በባንኩ ከተፈጸሙ የገንዘብ ግብይቶች 84 ነጥብ 5 በመቶው በዲጂታል የክፍያ አማራጮች መከናወኑንም ጠቅሰዋል።
የብድር አገልግሎት በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የባንኩ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው፤ በዘንድሮው የበጀት ዓመት ጠቅላላ የብድር መጠን ወደ 1 ነጥብ 35 ትሪሊየን ብር ማደጉን አስረድተዋል።
አዳዲስ የብድር ዓይነቶችን በተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ለደንበኞች በማስተዋወቅ የብድር ተደራሽነቱን ለማሳደግ እንሠራለን ማለታቸውን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ኤም.ሲ