
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በቶኪዮ እየተካሄደ በሚገኘው 33ኛው የእስያ፣ ዓረብ እና አፍሪካ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ የኢትዮጵያ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችን ፀጋ አስተዋወቀ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሐ ይታገሱ (ዶ/ር) መንግሥት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ቀልጣፋ፣ ሳቢ እና ተመራጭ ለማድረግ የወሰዳቸውን የፖሊሲ ማበረታቻዎች፣ ሀገር በቀል የሪፎርም ሥራዎችን እና በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖቹ ውስጥ ያሉ የአንድ መስኮት አገልግሎቶችን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ያላት ሰፊ ወጣት የሰው ኃይል ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ያደርጋታል ማለታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል።
በተጨማሪም በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና የነጻ ንግድ ቀጣና ውስጥ ያሉ መሠረተ-ልማቶች፣ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል በተመጣጣኝ ዋጋ ለኢንቨስተሮች መቅረቡ እና በዙሪያዋ ሰፊ የገበያ ዕድል መኖሩ ኢትዮጵያን ለዓለም አቀፍ ባለሃብቶች የበለጠ ተመራጭ መዳረሻ ያደርጋታል ብለዋል።
በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በበርካታ መመዘኛዎች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገር መሆኗን አስረድተዋል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ኤም.ሲ