
በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነትና ትብብር ኮሚቴ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የቢዝነስ ፎረም በዛሬው ዕለት በቤጂንግ ተካሂዷል።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው፤ የሁለቱን ሀገራት ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ኤምባሲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በመድረኩ ላይ ገልጸዋል።
በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ከ300 በላይ የቻይና ኩባንያዎች በፎረሙ ላይ የተሳተፉ ሲሆን በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በቱሪዝም ዘርፎች በኢትዮጵያ ያሉ ዕድሎችን በሚመለከት ውይይት ተደርጓል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮ-ቻይና የወዳጅነትና ትብብር ኮሚቴ በኢትዮጵያ ለመስራት እንቅስቃሴ እያደረገ ያለውን ‘‘ላይት አፕ ቪሌጅስ‘‘ ፕሮግራም በተመለከተ ገለጻ ተደርጓል።
በፎረሙ ላይ አንድ የቻይና ኩባንያ የይርጋጨፌ ቡና በመግዛት በቻይና ገበያ ‘አዲስካ ቡና’ በሚል ብራንድ ስም ለማቅረብና ለማስተዋወቅ እንዲችል የማብሰሪያ መርሀ ግብር መፈጸሙን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመልክቷል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ኤም.ሲ