የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከተጓዦችና የጭነት አገልግሎት ከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።
ማኅበሩ በየቀኑ ከ7 መቶ እስከ 1ሺህ ሰዎችን የማጓጓዝ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከ155 ሺህ በላይ ተጓዦችን እና 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን የጭነት አገልግሎት በማጓጓዝ የዕቅዱን 98 በመቶ ማሳካት መቻሉን የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ከ13 እስከ 15 በመቶ የወጪና ገቢ ምርት የሚያጓጉዘውን ማኅበር ከፈረንጆቹ 2024 ጥር ወር ጀምሮ ኢትዮጵያ የማስተዳደር ኃላፊነት ወስዳ እየሰራች መሆኗን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በባቡር ትራንስፖርት ምቹ ምኅዳር በመፍጠርም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የገቢና ወጪ ምርት የማጓጓዝ አቅም የበለጠ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ከ1ሺህ በላይ የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ ባቡሮች የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ምርት በማጓጓዝ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት እየደገፉ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ትራንስፖርት የሁለቱን ሀገራት ዜጎች በማገናኘት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝም አስረድተዋል።