በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በ14 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ወጪ የተገነባ ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧና መገጣጠሚያ ማማረቻ ፋብሪካ የፊታችን ቅዳሜ ይመረቃል።
ፋብሪካውን “ዜድ ኤም ትሬድ እና ኢንቨስትመንት” የተሰኘው ኢትዮጵያዊ የንግድ ኩባንያ እና የቻይናው ዓለም ዓቀፍ ድርጅት ሪፎ በጋራ እንደገነቡት ተገለጿል።
የፋብሪካውን ምርቃ አስመልክቶ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና የኩባንያዎቹ ከፍተኛ አመራሮች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ፋብሪካው በዘርፉ ያለውን የአቅርቦት እጥረት ለመፍታትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ያለመ ነው ተብሏል።
ፋብሪካውን ወደ ስራ ሲገባ 2ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ፒፒአር ትቦዎ እና 1 ነጥብ 9 ሚሊየን የፒፒአር መገጣጠሚያዎች ፣ 1 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የፒቪሲ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች እና 9መቶ ሺህ የፒቪሲ መገጣጠሚያዎች እንዲሁም 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሜትር በላይ የፒቪሲ ኮንዲዩት የማምረት ዓመታዊ አቅም አለው ነው የተባለው።
በዚህም በዘርፉ ያለውን የቧንቧ እና ቱቦ ዝርጋታ ስርዓት አቅርቦትና ጥራት እጥረትን ለመፍታት ያስችላል ተብሏል።
ፋብሪካው በአሁኑ ሰዓት የሙከራ ምርት እያመረተ ሲሆን ፥ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ለ600 በላይ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
በ3 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ፋብሪካው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧና መገጣጠሚያ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በመሆን እውቅና ማግኘቱም በመግለጫው ተመላክቷል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ