በሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም ብቻ ከ51 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚያዝያ ወር 51 ነጥብ 51 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 51 ነጥብ 07 ቢሊየን ብር ወይም የእቅዱን 99 ነጥብ 16 በመቶ መሰብሰብ መቻሉን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሯ ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ10 ነጥብ 65 በመቶ ወይም የ4 ነጥብ 91 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል።
በዚህም ባለፉት 10 ወራት 442 ነጥብ 85 ቢሊየን ብር ገቢ የመሰብሰብ ግብ ተጥሎ 425 ነጥብ 27 ቢሊየን ወይም የዕቅዱን 96 ነጥብ 03 በመቶ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።
ይህም አፈጻጸም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ54 ነጥብ 77 ቢሊየን ብር ወይም የ14 ነጥብ 78በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
ከተሰበሰበው ገቢ የሀገር ውስጥ ታክስ ድርሻ 271 ነጥብ 36 ቢሊየን ብር ሲሆን ቀሪው153 ነጥብ 91 ቢሊየን ብር ደግሞ ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ የተሰበሰበ መሆኑንም መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የገቢ አሰባሰቡ በየዓመቱ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም ከመንግስት የወጪ ፍላጎት፣ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ጥመርታ አንጻር አፈጻጸሙ ሲመዘን ገና ብዙ መሥራትን እንደሚጠይቅ አንስተዋል፡፡
ምንጭ፡ ኤፍ.ቢ.ሲ